……. አለ ዲጋ ሳቆ!



……. አለ ዲጋ ሳቆ!

             

ኮርማ ባጣ
አንገት አላጣ!
አለ ዲጋ ሳቆ የጆቴ አባት
መታያ እውነትን የገደለ ዕለት
ኮርማ ባጣ
አንገት አላጣ!
አለ ዲጋ ሳቆ የኖሌ አባት  
ያገር ዳኞች የዋሹ ዕለት
የሲቃ ዕለት  …የእልህ ቀን
እኔው ነኝ ኮርማ  …እኔው ነኝ ወይፈን”!
አለ ዲጋ ሳቆ የጆርጎው ሰው
የሱ እልሁ እኩያ የለው
        ***
መዳፍ ታክል ትንሽ ኩሬ
ለከብት ሆራ ለሰው አውሬ
መሀል ድንበር ተሸንቁራ የምትገኝ
ያም የኔ ናት  ያም የኔ ናት  የምታሰኝ
ወይ ለዚህኛው ወይ ለዚያኛው ያልተገባች
የእገሌ ሆራ ያልተባለች
የጸብ መንስኤ የነገር ምንጭ
ህዝብ አዋኪ አገር በጥባጭ
ሰላም ነስታ እያወከች
ሁለት ሞቲ ታፋጃለች።
ነጋ ጠባ፤ ዓመት ካመት
ሁለት ሞቲ እንደ ጠላት  
አይናገር፤ አይወያይ፤ አይዋደድ
ሆኖ ይኖራል ጀርባና ሆድ።
                ***
ይህ ነገር እንዲቆረጥ ጠቡ እንዲፈርስ
ሰላም ሰፍኖ ፍቅር እንዲነግስ
እውነት ከመንበሩ እንዲመለስ
ሞቲዎቹ እንዲታረቁ
ያገር ዳኞች የታወቁ
ከባህሉም ከትውፊቱም የተመገቡ
ከዕድሜና ከልምድ የጠገቡ
ፍትህ፤ ርትዕ፤ የማያዛቡ
ናቸው ተብለው የሚታሰቡ
ይህን ችግር እንዲመዝኑ
የመፍትሄ ሀሳብ እንዲወስኑ
ለፍትህ ብቻ እንዲበይኑ፤
ለማንም ሰው ሳያዳሉ
አዛውንቶች ይህን ሲሉ
ሞቲዎችም ይሁን አሉ
ይህን ሀሳብ ተቀበሉ
በዚህ ስሌት ያገሬው ሰው ኦዳ ጥላ ስር ተቀምጦ
ተወያይቶ፤ ብዙ መክሮ፤ ተነጋግሮ፤ ዳኞች ሰየመ መርጦ።
       ***
ያገር ዳኞቹም ላያዳሉ
በዋቃ ፊት መሀላ ማሉ
ያገሬው ህዝብ በታላቁ የኦዳ ዛፍ
ስር ተቀምጦ ከጫፍ እጫፍ
መሀላ ሰማ ከአዛውንት አፍ፤
እንዲህም ሲሉ
በዋቃ ፊትም ማሉ፤
  ልጄ ይሁን የውሻ ልጅ
 ደጄ ይሁን ያሳማ ደጅ
         እውነት ላልክድ ሀቅ ላላፈርስ
         እውነት ብክድ የኔን ቄዬ እባብ ይውረስ 
እንድህ ብለው መሀላ ማሉ
ሰላም ሊያነግሱ ሳያዳሉ።
***
ሆኖም…….  መች  ሰላምን አነገሱ
ይልቅስ እውነትን አድበሰበሱ
በመታያ መሀላ አፈረሱ!
ለካ…….  ሌላው ሞቲ ከዲጋ ሳቆ ተሰውሮ
በሽፍን ሽፍንፍን እጅ ወርቅ ሰቶ ኖሮ
ያገር ዳኛም መሀላውን አፈረሰ በወርቅ ሰክሮ።
ዕውነትን ክዶ ግፍ አነገሰ    
ወርቅ ለሰጠው ምስጥር ተነፈሰ
በጆሮው ምክር አጎረሰ፤
 “አስቀድሞ ለዚህ ሆራ እርድ የለገሰ
  ወይም ደም ያፈሰሰ
ለሱ ይሁን እሱ ይውሰድ
ይህ ይሆናል የእኛ ፍርድ
የሚያዋጣህን አንተው ዘይድ
ይሄ ምስጥር እንዳይዛመት ካንተ ሌላ
ቃልክን ስጠነ በመሃላ፤
በመታያ የሰከረ እንድህ ብሎ መከረ
መሃላውንም፣ ሀቅንም ሰበረ።
        ***

የብይን ዕለት ህዝብ መጥቶ ኦዳ ግርጌ ተቀመጠ
ብይን ሊያዳምጥ እውነት ሊሰማም ቋመጠ
ያገር ዳኛ እንደመከረ
እንድህ ብሎ በአንድ አፍ ተናገረ
 “አስቀድሞ ለዚህ ሆራ እርድ የለገሰ
  ወይም ደም ያፈሰሰ
ለሱ ይሁን ይሄ ሆራ
ይሄ ጉዳይ ሁለተኛ አይነሳ፤ አይወራ
ሞቲዎችም ካሁን ወድያ እንዳትሆኑ ባላጋራ።
አለና ብይኑን አብራራ
ረችው ሞቲም ፎከረ፤ አቅራራ
         ይህ ሆራ ከጥንቱ ከጠዋቱ
         የኔ እኮ ነው በእውነቱ
         ምን ይባላል ዲጋ ሳቆ አጉል ሙግት መሞገቱ?
         በሉ ልጆች ያንን ኮርማ ወዲህ አምጡ!
አለና ለልጆቹ ትዕዛዝ ሰጠ በትዕቢት ተወጥሮ
የሳቆም ልጅ እጅግ አምርሮ
         ወይኔ ዲጋ ተታለልኩኝ
         የአባቴን ሆራ ተዘረፍኩኝ
ብሎ ሊጮህ አስቦ ዲጋ
ሆኖም አደብ ገዛ ተረጋጋ።
***
የእርድ ኮርማም ቀረበ
በገመድ እዬተሳበ
ረችው ሞቲም ሊያርድ ጣለው
ዲጋ ሳቆን ምን ይዋጠው
ጥሎ እንዳያርድ ኮርማ የለው
ኮርማ የለው እግዚኦ ጣጣ
ቢሆንም ግን አንገት አያጣ!
ትዕግስቱን ቋጠረና
ወደ ህዝብም ዞር አለና
ግንፍል ስሜቱን አምቆ
ንዴቱን በትዕግስት አንቆ
እንድህ አለ ዲጋ ሳቆ:
         መልካም ነበር ኮርማ ጥዬ ደም ባፈሰስኩ
        ሆኖም ስለ ኮርማም ስለ ደምም አልተነገርኩ
        የሰማይ እውነት የምድር እውነት ይይብኝ 
ማንም ዳኛ አልነገረኝ
        የእርድ ኮርማ ከዚህ የለኝ
        እጫካ ውስጥ አልደበቅኩኝ
ወደ ረታው ሞቲም ዞረ አለና
ሳጉን ውጦ ከደረቱ ቀና አለና
           እሾ ጉርባ! እሰየው! እንኳን ረታህ!  
           እሰይ! እንኳን ረታህ! እንኳን በለስ ቀናህ!
ለምድር ለሰማይ የከበዱ
የኛው ዳኞች ከፈረዱ
በነሱ ፍርድ መሰረት
ሆራው ያንተ ነው ምናልባት
        ስለዚህ ተረከበኝ ይሄውልህ የጬካ ዘንጉ
        የእረኛ ልምድ፤የአርቢና፤ የርቢ ወጉ
        ምን ሊረባኝ ካሁን ወዲያ መለፍለፉ    
አውቃአለሁ የኔ ላሞች እንደነጠፉ
ያንተ ላሞች እንዳጋቱ
የኔ ተስፋዎች እንደሞቱ
ያንተ ሚስት በቅቤ ተለቅልቃ ስትወዛ  ስትቀባ
የኔ ሚስት በንጣት አመዳም ሆና ነጫጭባ
የኔ ልጆች በባዶ ሆድ ሲተኙ
ያንተ ልጆች ወተት እየዋኙ
ያንተ ጎሳ ባለ በረት
የኔ  ጎሳ ባለ ኮተት
ምን ሊፈይደኝ የጬካ ዘንጉ
አንተ ውሰደው ከነ ወጉ
ከነክብሩ  ከነማእረጉ
ያንተ  ልጆች ወዛም
የኔ  ልጆች  አመዳም
ያንተ ከብቶች ደንዳና
የኔ ከብቶች ኮስማና
አንተ ቤት ቅቤ እንደ ጎርፍ
እኔ ቤት ከማንኪያ አያልፍ
ያንተ ነገ ብርሃናማ
የኔ ነገ ጨለማ
ምን ሊፈይደኝ የጬካ ዘንጉ
አንተ ውሰደው ከነ ወጉ
ከነክብሩ  ከነማእረጉ
ለምድር ለሰማይ የከበዱ
ያገር ዳኞች ከፈረዱ
በነሱ ፍርድ መሰረት
ሆራው ያንተ ነው ምናልባት 
ተረከበኝ የጬካ ዘንግ
ወስደህ አኑራት ከበረት ጥግ
***
ወደ ዳኞቹም ዕይታውን እያዞረ
          ይህ ስራችሁ እንኳን ሰመረ
         ሆኖም ኮርማ የለኝ ደም አላፈስ
         ፍትህ አጥቼ ወደ ቤቴ አልመለስ
         ደም አፍስሶ ሆራ ማግኘት ከተቻለ
         የኔ ደም አይፈሰም ማነው ያለ?
  እንደ ጎርፍ ጎርፎ ይህን ግፍ አጥቦ ካፀዳ
  የኔው ደም እንደ ውሃ ይቀዳ!
   የሲቃ ዕለት የእልህ ቀንማ
እኔው ነኝ ኮርማ እኔው ነኝ ኮርማ!
ኮርማ ባጣ
አንገት አላጣ!
ደም አፍስሶ ሆራ ማግኘት ከተቻለ
         የኔ ደም አይፈስም ማነው ያለ?
ጎርፍ ሆኖ ይህን ግፍ አጥቦ ካፀዳ
  የኔው ደም እንደ ውሃ ይቀዳ!
  ይፍሰስና መድልዖን ያጽዳ!  
ይህንና ብዙ እሮሮ ሌላም ሌላም ካለ በኋላ
ሳይታሰብ ጎራዴውን መዘዘና አንገቱን ቀላ!
***
ኮርማ ባጣ
አንገት አላጣ!
አለ ዲጋ ሳቆ የጆቴ አባት
መታያ ሀቅን የገደለ ዕለት
ኮርማ ባጣ
አንገት አላጣ!
ብሎ አለና ዲጋ ሳቆ ሰውዬዋ
ለእፍኝ ሆራ ራሱን ሰዋ!
         ***
ኮርማ ባጣ
አንገት አላጣ!
አለ ዲጋ ሳቆ የኖሌ አባት 
ያገር ዳኞች የዋሹ ዕለት
የሲቃ ዕለት  …የእልህ ቀን
እኔው ነኝ ኮርማ  …እኔው ነኝ ወይፈን”!
አለ ዲጋ ሳቆ የጆርጎው ሰው
የሱ እልሁ ዕኩያ የለው
ዲጋ ሳቆ ዘመዶች

ድርሰት              ዘለዓለም አበራ ተስፋ            
ታህሳስ 5/ 1999· ታምፔሬ ፊንላንድ

ትርጉም              ዘለዓለም አበራ ተስፋ   
                       ጥር 12 2018·  ሄልሲንኪ ፊንላንድ



Comments

Post a Comment

Popular posts from this blog

Geerarsaa: A Multifaceted Genre of the Oromoo Oral Art

Hooda Rirriittu eele / የማሰሻው ትንግርት

The Repertoires and Social Roles of Oromoo Asmaarii’s Performance