እይታ ለግሌ

                                 ዘለዓለም አበራ ተስፋ

                                            11.07.2021  

ለሰው ማዬት ቢሰለቸኝ

ለግልዬ አዬሁልኝ

አየሁልኝ ብዙ ነገር

የተፈጥሮን ድንቅ ምስጥር

ተረተሩ ሲተረተር

ወናፍ አየር ምጎ ሲወጠር

ኘስስስ ሲል … ተፍቶ አየር

ፍቅር ጥላቻን ሲያመር

ጥላቻ ፍቅርን ሲያመር

ቁንጫ ቁንጭትን ሲሰር

ትንኝ  ትንኝትን ሲያበር

ሸረሪት ድሩን ሲያከር፣

አስመሳይ የሌሊት ወፍ

ከወፎች ጋር እንደ ወፍ

ክንፉን ዘርግቶ ሲከንፍ

ካይጦችም ዋሻ ሲወተፍ

የስጋ ዝምድና ሊቀፍ

አየሁ፣ መቼም ዓይን አያርፍ፣

ያኛው ሲሔድ ይህ ሲመጣ

ከፍ አልኩ ሲል ሲቀናጣ

ሲንጠለጠል እንደ ቋንጣ

ከላይ ሆኖ ስም ሲያወጣ

ስም አለቀ ከዬት ያምጣ

ለሱ የሚሆን ስም እስኪታጣ

አቦ ስንቱን አየሁ አቤት ጣጣ፣

የሰው አንጆ እርጥብ ስጋ

ለሁሉ ኣድር ባይ የሰው መንጋ

እነሳቸው አ አክ ሲሉ የሚንጋጋ

እንዲተፉበት የጅ መዳፉን የሚዘረጋ

የመቤቱ ውታፍ ነቃይ

ለጌቶቹም ታማኝ ነኝ ባይ

ወሸከሬ የሰው አውደልዳይ

በሳሎንም ባደባባይ፣

ኧረ ስንቱን አዬሁ በግላጭ

አይጠ-ሞገጥ ከቋጥኝ ሲጋጭ

በቂጡ ወድቆ  ሲንዘጭ

ባለቅኔው ሲቀነቅን ሲቀኝ

ባላንጣዬ  እንድጨልም ሲመኝ

እምቢ ብዬ በራሁልኝ ።

“የዳመና አመልማሎ

ከሰማይ ዳገት ተንከባሎ

ሲጠጥር እንደ አሎሎ

ሲንከራተት ውሃ አዝሎ

በምላሰ-ጣት ተፈትሎ

ለታረዘ ሁሉ ቡልኮ”

ሆነ በል ይለኛል እኮ!

ከዝያማ…..“አገር ምድሩን እያለበሰ

ጅረት ሆኖ ሞልቶ ፈሰሰ”

ብለህ በል ሲለኝ እምቢ አልኩልኝ።

አሳይዬ  ሳያሳየኝ

ነጋርዬ ሳይነግረኝ

እኔው ለኔ ነገርኩልኝ።

 ሌላው ታናሽ እሱ ታላቅ

እሱ ርኅሩኅ ሌላው ጭራቅ

ሌላው ቡቡ እሱ ብራቅ

ሲገለጥ ግን ቆዳው ሲፋቅ

እንደሆነ አጉል ስላቅ

ብዙ ነገር አየሁልኝ

አንጡራዬን ለየሁልኝ

እኔው ለኔ በራሁልኝ

እኔው ለኔ ተገለጥኩልኝ

ነቃ ብዬ ቆምኩልኝ

ግልዬን ወድጄ ወደኩልኝ

ለግልዬ በሞትኩልኝ።

 

              ዘለዓለም አበራ ተስፋ

                ሔልሲንኪ / ፊንላንድ 

Comments

Post a Comment

Popular posts from this blog

Geerarsaa: A Multifaceted Genre of the Oromoo Oral Art

Hooda Rirriittu eele / የማሰሻው ትንግርት

The Repertoires and Social Roles of Oromoo Asmaarii’s Performance